Description
ጂብራን ካህሊል ጂብራን (Gubran Khalil Gubran) እ.ኤ.አ ጥር 6 ቀን 1883 ዓ.ም. ከማሮናይት ካቶሊክ ቤተሰብ ቢሻሪ፣ሊባኖስ ተወለደ። አባቱ ጂብራን ለእናቱ ከሚላ ሦስተኛ ባል ሲሆን የአባትየው ያልተገባ ባህርያትና ብኩንነት መላ ቤተሰቡን ለድህነት ዳርጐታል።
በዚሁ የአባቱ ብኩንነት የተነሳ ጂብራን መደበኛ ትምህርት መከታተል አልቻለም ነበር። በልጅነት ዕድሜው ደጋግመው ከጐበኙት ቀሳውስት ሥር ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ፣አረብኛና በርከት ያሉ የሶሪያ ቋንቋዎችን ተማረ። አባቱ በማጭበርር ወንጀል ከታሠረ በኋላ የጂብራን ቤተሰብ ሙሉ በሙሉ አደጋ ላይ ወደቁ። እናቱ ከሚላም እ.ኤ.አ በ1895 ዓ.ም. ካህሊልንና ወንድሙ ጴጥሮስን፤እንዲሁም እህቶቹ ማሪና እና ሱልጣናን ይዛ ወደ አሜሪካ ተሰደደች።
ቤተሰቡ ቦስተን ከደረሰ በኋላ ጂብራን ትምህርት ቤት ተመዘገበ። በስህተት ‘ካህሊል ጂብራን’ በሚል ስሙ ትምህርት ቤት ከተመዘገበ በኋላ ይህ ስም የቀጣይ ዘመናት መለያው ሊሆን ቻለ። በአጭር ጊዜ የትምህርት ቤት ቆይታውም የሁለገቡን አርቲስት ፍሬድ ሆላንድ ዴይ ቀልብ ሳበ። በእርሱ መምህርነትም ሕይወቱ ማበብ ቻለች።
እናቱ ከሚላ በዚህ አልተደሰተችም። ልጇ በምዕራቡ ዓለም ባህል መዋጡ ስላሳሰባትም የራሱን ባህልና ታሪክ ይማር ዘንድ ወደ ቤሩት መልሳ ላከችው።
ወደ አሜሪካ ከተመለሰ በኋላ የሥዕል ሥራውን ካቆመበት ቀጠለ። በሃያ አንድ ዓመት ዕድሜውም የመጀመሪያ ዐውደ-ርዕዩን አሳየ። ከዚያም በመጀመሪያ በአረብኛ ከዚያም በእንግሊዝኛ የተለያዩ ጽሑፎችን ማስነበብ ቀጠለ። የአረብና ምዕራቡን ዓለማት ያዋሃደው አጻጻፉም የዝና መንገዱን ከፈተለት።
ካህሊል ጂብራን ከሠዓሊነቱ ይልቅ በደራሲነቱ ይበልጥ ቢታወቅም ቅሉ ከ700 በላይ ሥዕሎችን ስሏል። ብዙ ዕድሜውን በአሜሪካ ከማሳለፍ ይልቅ ጂብራን ወደ አገሩ እየተመላለሰ በመኖር ሊባኖሳዊ ዜግነቱን ሳይለቅ ኖሯል። የአገሩና የሕዝቡም በጐነት ለልቡ ቅርብ ነበሩ።










Reviews
There are no reviews yet.